የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ሎጂስቲክስ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሸያ ካውንሥል ማን ነው?

የኢፌድሪ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ካውንስል በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር ጥር 12 ቀን 2012 ዓ.ም የኢፌድሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ካውንስል በሚል መጠሪያ የተቋቋመና በቀድሞ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አስር ተጠሪ ተቋማት፡ የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት ፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ፣ የኢትዮጵያ ማሪታም ጉዳዮች ባለስልጣን ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰረቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ሲፈትሽ፣ ሲከታተል እና ድጋፍ ሲሰጥ የነበረ ካውንስል ነው፡፡ ይህ ካውንስል በተገልጋዮችና በሚኒስትሪው በኩል እንደ ጠንካራ ድልድይ፣ እንደ ጥሩ አይንና ጆሮ በመሆን የሚሰጡ አገልግሎቶችን በመዳሰስ አገልግሎቶች ጥራትና ይዘታቸው የሚያድግበትና የሚሻሻልበትን መንገድ በመጠቆም ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ይህ ካውንስል ስልሳ ዘጠኝ (69) አባል ተቋማትን የሚወክል እና በውስጡ ዘጠኝ (9) ስራ አስፈጻሚ አባላትን የያዘ ነው፡፡

በ2013ዓ.ም የተደረገውን ሃገራዊ ምርጫ ተከትሎ በተደረገው የመንግስት የአደረጃጃት ለውጥ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ስያሜውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በሚል የቀየረ ሲሆን በሚኒስትሪው ስር ያሉት ተጠሪ ተቋማትም ከአስር ወደ አምስት ተቀንሰዋል፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰረቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት፣ ኢትዮ- ጅቡቲ ባቡር እና የኢትዮጵያ ማሪታም ጉዳዮች ባለስልጣን ሲሆኑ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ደግሞ ከሚኒስትው ጋር በይፋ ተቀላቅሏል፡፡

ይህንን አዲስ የአደረጃጀት ለውጥ ተከትሎ የቀድሞው የኢፌድሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ካውንስል የኢፌድሪ ትራስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ካውንስል በሚል አዲስ ስያሜ የቀደመውን አላማ አንግቦ በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር ባሉ አምስት ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰረቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት፣ ኢትዮ- ጅቡቲ ባቡር እና የኢትዮጵያ ማሪታም ጉዳዮች ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት የሚደግፍ፣ የሚፈትሽ እና አገልግሎቶች ጥራታቸውን ጠብቀው ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ተደራሽ መሆን እንዲችሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ካውንስል ነው፡፡

ይህ ካውንስል በትራንስፖርት ዘርፉ ውስጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት በቀጣይነት ለማሻሻልና ከተገልጋዩ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ተገልጋዩ ህብረተሰብ በተገቢው ደረጃ መሳተፍ እንዳለበትና አጀንዳውን በባለቤትነት ይዞ ለተፈፃሚነቱ መረባረብ እንዳለበት ያምናል፡፡ በመሆኑም የህዝቡን ንቁ ተሣትፎ የሚጋብዝና ፍትሀዊ ተጠቃሚነቱንም የሚያጐለብት እንዲሁም ከዚህ ቀደም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲሰራበት የነበረውን የአሰራር ማእቀፍ ይዘትና በትግበራው ላይ የተስተዋለውን ክፍተት ለመቅረፍ እንዲያግዝ ከተጠቃሚው ህብረተሰብ አገልግሎት አሰጣጡን በተመለከተ አስተያየት ለመሰብሰብ ለለውጥ በግብአትነት ለመጠቀም ይህ ድረ-ገጽ ተከፍቶ በስራ ላይ ውሏል፡፡

አላማ

 1. የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች የሚመረመሩበት መድረክ እና ለመንግስት የሚቀርቡበት ድልድይ ሆኖ ማገልገል፡፡
 2. በዘርፉ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለይቶ በማውጣት መፍትሄው ላይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር መስራት
 3. ህብረተሰቡ በዘርፉ ባሉ የአገልግሎት አሰጣጦች ዙሪያ የተሰማውን ሃሳብ አስተያየት እና ቅሬታ የሚያቀርብበት መድረክ መሆን ወይም መፍጠር
 4. የአባላትን ፍላጎት መወከል፣ መጠበቅ እንዲሁም አብሮነትና መተባበርን ማጠናከር ፤
 5. ዘርፉን የሚመለከቱ ረቂቅ ሕጎች እና መመሪያዎች ላይ ግብዓት መስጠት
 6. በመላ አገሪቱ መልካም የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ማጎልበት
 7. የተለያዩ ጥናቶችን በማከናወን የህብረተሰቡን ችግር በጥልቀት ለመረዳት መሞከር

የካውንስሉ ተልዕኮ

ከትራንስፖርት ሚኒስቴር በተሰጠው ተግባርና ሃላፊነት መሰረት ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ከተጠሪ ተቋማቱ ማግኘቱን በማረጋገጥ እንዲሁም በተጠሪ ተቋማቱና ስራውን በሚተገብሩ የግል ዘርፉ መካከል ያለውን ግንኙነት ቀልጣፋ በማድረግ የዘርፉን ችግሮች በጋራ በመፍታት ተልኮውን ማሳካት፡፡

 • ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት
 • የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰረቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት
 • የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን
 • የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት
 • የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን
 • የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት